Thursday, November 10, 2016

ደብረ ምህረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ሰንበት ት/ቤት፤ጎንደር መንበረ ጵጵስና


  • የሰንበት ት/ቤታችን አባል ይሁኑ
  • ደብረ ምህረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት
  • ነገረ ሃይማኖት
  • ነገረ ሥላሴ
  • ነገረ ማርያም
  • ነገረ ቅዱሳን
  • የቤ /ን ታሪክ
  • ወቅታዊ ጉዳዮች
  • ዜና ደብረ ምህረት
  • ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች
  • ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ ጉዳዮች ይከታተሉ!!!#


Thursday, May 12, 2016

"ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ"

ሚያዝያ21/2008ዓ.ም
  •  ‪‎በዚች‬ ዕለት በአምላካችን ላይ የተፈጸመው መከራ እጅግ አሰቃቂና በፍጡር ሊገለጸ የማይችል ነው፡፡ ‪
  • ‎የክብርን‬ ባለቤት ጭፍሮች ይዘው በሊቀ ካህናቱ ፊት አቀረቡት፡፡ሊቀ ካህናቱም ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንክ ንገረኝ ››አለው ጌታም ‹‹ አንተ አልህ…የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ ›› ሲለው ሊቀ ካህናቱ ‹‹ተሳደበ›› በማለት ፊቱን ነጨ ልብሱን ቀደደ፡፡በኦሪት ሕግ እንዲህ ያደረገ ሊቀ ካህን ይሻር ትል ነበር፡፡ጌታ እንደተሸመበት እርሱ እንደተሻረበት ለማጠየቅ፡፡ ማቴ26፤57-65.ማር14፤47-54፣ሉቃ22፤47-54፣ ዮሐ18፤1-24 
  • ‪ጌታ‬ እንደተናገረው ጴጥሮስ ሦስተጊዜ ካደው በዚህም ጊዜ ደሮ ጮኸ ፡፡ጴጥሮስም ጌታ ያለውን አስታውሶ እንዲህ ሲል አለቀሰ ‹‹ ከሁሉ ይልቅ እወደው ከሁሉ አስቀድሞ እኔ ልካደው›› ብሎ ከልቡ ስላለቀሰ ንስሐውን ተቀብሎለታል፡፡ ማቴ26፤69-75፣ ማር14፤67-72፣ሉቃ22፤ 55፤62፣ዮሐ18፤25-27     
ዓርብ በነግህ/አስራ ሁለት ሰዓት/
  •  ‪በፍጥረታት‬ ሁሉ ላይ የሚፈርደው ሰማያዊ ንጉስ ለፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡ ‪#‎ጲላጦስም‬ መርምሮ ለሞት የሚያበቃ አንዳች አጣበት ሕዝብ ግን ስቀለው ስቀለው እያሉ አብዝተው ጮኹ፡፡አብሮቅላ የተባለችው የጲላጦስ ሚስት ክፉ እንዳያደርግበት ለባለ መልዕክት ላከች ስለእርሱ በህልሟ ስትሰቃይ አድራለችና፡፡
  • ጲላጦስም ክርስቶስ የገሊላ ሰው መሆኑን ሲረዳ የገሊላ ገዥ ወደ ሆነው ሄሮድስ ሰደደው፡፡ጲላጦስና ሄሮድስ እኔ ልግዛ እኔ ልግዛ እያሉ በዳኝነት ይጣሉ ነበር አሁን ግን በጌታ ሞት ታረቁ፡፡ሄሮድስም መልሶ ለጲላጦስ መለሰለት፡፡ለእስራኤላውን ፋሰካ በዓል ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበት ነውና በዓመት በዓመት የሚፈልጉትን እስረኛ ሊፈታላቸው ልማድ ስለነበራቸው በርባን የተባለውን ወንበዴ እንዲፈታላቸው ጠየቁት እርሱ ግን ኢየሱስን ልፍታላችሁ ወይስ በርባንን ቢላቸው ወንበዴዎን በርባንን መረጡ፡፡ወንበዴው ተፈቶ እርሱ መሞቱ ስለ ኃጢአተኞች እንደሆነ የሚያስተምር ነው። ማቴ27፤1-10፣ማር15፤ 1-5፣ሉቃ23፤1-56፣ዮሐ18፤28-38
ሦስት‬ ሰዓት/ ተገረፈ/ ‪
  • ጲላጢስም‬ መርምሮ ወንጀል አጣበት ሕዝቡ ግን ስቀለው እያሉ መጮሃቸውን በቀጠሉ ጊዜ ቢገረፍ ልባቸው ይራራ ይሆን በማለት አስገረፈው፡፡እነርሱ ግን እንኳን ሊራሩ አርባ ጅራፍ ብቻ መግረፍ ሲኖርባቸው እየተፈራረቁ ክንዳቸው እስኪዝል ስፍር ቁጥር የሌለው ጅራፍ 6666 ጊዜ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪታይ ገረፉት፡፡ ጲላጦስም ለስልጣኑ በመፍራት ንጹህ እንደሆነ እጁን በመጣጠብ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰታቸው። ማቴ27፤24-26፣ማር15፤6-15፣ ሉቃ23፤1-26፣ዮሀ18፤28-38
 ‪‎ስድስት‬ ሰዓት/ተሰቀለ/ ‪
  • ሱራፌል‬ እና ኪሩቤል ያለ ማቋረጥ የሚያመሰግኑት ክፉዎች አይሁዶች ዘበቱበት፣መላእክት የሚሰግዱለትን ተፉበት፣መቃን ይዘው ራሱን መቱት ከዚህ በኋላ ለመዘባባት ያለበሱትን ቀዩን ግምጃ ገፈው ወደሚሰቅሉበት ቀራንዮ ከባድ እጸ መስቀል አሸከሙት ፡፡ ከባዱን ዕፀ መስቀል መሸከሙ ከባዱን ኃጢአታችንን እንደተሸከመ የሚያጠይቀ ነው፡፡ቅ.ጴጥሮስ ‹‹ ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ ›› እንዳለ 1ጴጥ2፤22፡፡
  •  ‪#‎ስምኦን‬ የተባለ የቀሬና ሰው ነገር ፈርቶ ተሰውሮ ውሎ ነገር ተፈጽሞ ይሆናል ብሎ ሲመለስ አገኙትና አንተም የእርሱ ወገን ነህ መስቀሉን ተሸከም ብለው አሸከሙት ምስጢሩ ግን ጌታ ከበረከተ መስቀሉ ሊያሳትፈው ስለፈለገ ነበር፡፡ማቴ27፤27-31፣ማር15፤16-20፣ ሉቃ23፣26-30፣ዮሐ19፤17 
  • ‪#‎ወንበዴ‬ እንዲመስላቸው ‹‹ ደግ አደረጉ የስራውን ነው እንዲሉ››በግራና በቀኝ ወንበዴዎችን አድርገው ሰቀሉት፡፡ኢሳኢያስ በትንቢት‹‹ ከአመጸኞች ጋር ተቆጠረ››ያለው ተፈጸመ፡፡ ኢሳ53፤12 ‪#‎ጌታችን‬ በፍጹም ያፈቀረውን የሰውን ልጅ ሊክስ መጥቷልና ወደ ዕጸ በለስ የገሰገሱ የአዳምን እግሮች ለመካስ እግሮቹ ተቸንክረው ዋሉ፣የበለስን ፍሬ የቀጠፉ እጆቹን ለመካስ እጆቹ ተቸንክረው ዋሉ፣ጣፋጩን የበለስን ፍሬ መቅመሱን ለመካስ መራራ ሐሞት ቀመሰ፡፡ 
  • #‎ጲላጦስ‬ አይሁድ ተመቅኝተው ለሞት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበርና ‹‹የአይሁድ ንጉስ የናዝሬቱ ኢየሱስ ›› የሚል ጽሁፍ በሦስት ቋንቋ በጽርዕ/ግሪክ/፣በዕብራይስጥ፣በሮማይስጥ በመጻፈ መስቀሉ ላይ አኖረ፡፡ማቴ26፣37፣ማር15፣27፣ሉቃ23፣38፣ዮሐ19፣19-22፣ 
ዘጠኝ‬ ሰዓት /ሞተ
  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስራ ሦስት ሕማማተ መስቀል ከተቀበለ በኋላ የሰው ልጅ ያጣውን ሕይወት በሞቱ ለመካስ መራራ ሞትን በፈቃዱ ተቀበለ፡፡ነቢዩ ኢሳኢያስ ‹‹ እግዚአብሔር የሁላችንን በደል በርሱ ላይ አኖረ ተጨነቀ፣ተሰቃየ፣አፉንም አልከፈተም ለመታረድም እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም ከኃያላን ጋር ምርኮን ይካፈላል ነፍሱንም ለሞት አሳልፎ ሰጥቷልና፡፡››ኢሳ52፤6-12/ #ጌታችን ‹‹ ነፍሴን ስለ በጎቸ አኖራለሁ ››ዮሐ1፤16 ባለው መሰረት በዕለተ አርብ በአውደ ቀራንዮ በዘጠን ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በፈቃዱ እንዲህ በማለት ለአባቱ ሰጠ ‹‹ አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ፡፡ ጌታችንም ከመመቱ አስቀድሞ ሰባቱ አጽርሐ መስቀል ተናግሯል፡፡ እነርሱም 
፩. ኤልኼ ኤልኼ ላማሰበቅታኒ/አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ።ማቴ27፤36 ጌታችን እንዲህ ማለቱ በደካማነት ወይም መለኮት ስለተለየው ሳይሆን ለኛ መከራ በገጠማችሁ ጊዜ ጸልዩ በማለት አብነት ሊሆን ነው፡፡አንድም ዲያቢሎስ በአካለ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን እንዳሳተው ክርስቶስ ዳካማውን የአዳምን ሥጋ ለብሶ በደካማነቱ ቢጠጋው ድል እንደነሳው ለማስተማር ነው፡፡/ለአቅርቦተ ሰይጣንና የሰይጣንን ጥበብ በጥበቡ ለመሻር/
፪.‹‹ አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ ››/አባት ሆይ የሚያደረጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ሉቃ23፤24 ፡፡ከስቅለቱ ሳያውቁ የተሳተፉ አሉና ከስቅለቱ ሲለይ ይህንን ተናገረ፡፡
፫. ዮም ትሄሉ ምስሌየ ወስተ ገነት ›› /ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ/ ›› ሉቃ 23፤33 
፬. ‹‹ አባ አመሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ ›› /አባት ሆይ ነፍስ በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ሉቃ 23፤46 
፭. ‹‹ ነዋ ወልድኪ ነያ እምከ ››/ እንሆ ልጅሽ እንኋት እናትህ/ ዮሐ19፤26-27 
፮. ‹‹ ከመ ይብጻሕ ቃለ መጽሐፍ ዘይቤ ጻማዕኩ ›› / መጽሐፍ በመብሌ ውስጥ ሐሞት ጨመሩበት /መዝ68፤21/ ያለው ይፈጸም ዘንድ ተጠማሁ አለ። ዮሐ19፤28 
፯. ‹‹ ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ ›› የተነገረው ተስፋ የመሰለው ምሳሌ የተተነበየው ትንቢት ደረሰ ተፈጸመ ሲል ተፈጸመ አለ፡፡ዮሐ19፤30 ከዚህ በኋላ ቅድስት ነፍሱ ከስጋው ስትለይ አምላክነቱን ለመግለጽ በምድር አራት በሰማይ ሦስት ተአምራቶች ታይተዋል ፡፡ 
እነርሱም በምድር ፤-
፩-የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ፣ 
፪-ምድር ተናወጠች፣
፫-አለቶች ተሰነጣጠቁ፣ 
፬-መቃብሮች ተከፈቱ፣ሙታን ተነሱ፡፡ ማቴ27፤51-53 በሰማይ ፤- ፩- ፀሐይ ጨለመች፣ ፪-ጨረቃም ደም ሆነች፣ ፫-ከዋክብት እረገፉ፡፡ማቴ27፤35
አስራ‬ አንድ ሰዓት/ ተቀበረ/ ‪
  • የአይሁድ‬ ፋሲካ ቀርቦ ነበር እና ሥጋቸው በመስቀል እንዲይውል ጭናቸው ተሰብሮ እንዲሞቱ ጲላጦስን ለመኑት እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ጌታን ሊሰብሩት ሲመጡ ሞቶ አገኙት በዚህ ጊዜ ሌንጊኖስ የሚባል ወታደር መሞቱን ሊያጣራ ጎኑን በጦር ሲወጋው ከጎኑ ደምና ውሃ ፈሰሰ ይህም የምንጠመቅበት ማየ ገቦ ነው፡፡ በሥውር የጌታ ተማሪ የሆነው የአርማትሱ ዮሴፍና የአይሁድ አለቃ ኒቆዲሞስ ሥጋውን ለጲላጦስ ለምነው በማስፈቀድ እንደ አይሁድ የአገናናዝ ሥርዓት በሽቶ ጋር በተልባ እግር አልብሰው ‹‹ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ›› እያሉ ገንዘው ማንም ባልተቀበረበት አዲስ መቃበር ቀበሩት፡፡ምነው ቅዱሳን ነቢያት ባረፉበት መቃበር ያልተቀበሩ ቢባል ኋላ በትንሳኤው ሲነሳ የነቢያት አጽም አስነሳው እንጂ መቼ በስልጣኑ ተነሳ ባሉ ነበርና እንዲያ እንዳይሉ በአዲስ መቃበር ተቀበረ፡፡ማቴ27፤57-6 1፣ማር15፤42-47፣ሉቃ23፤50-56፣ዮሐ 19፤32-40

Wednesday, March 23, 2016

የኢትዮጵያ‬ ቤተ ክርስቲያን ሥያሜ

ጥንታዊት‬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ›› በመባል ትታወቃለች፡፡ኦርቶዶክስ የሚለው ‹‹ኦርቶ›› እና ‹‹ ዶክስ›› ከሚሉት ሁለት የግሪክ ቃላት የተወሰደ ነው፡፡‹‹ኦርቶ››  ማለት ቀጥተኛ የተስተካካለ ማለት ሲሆን ‹‹ ዶክስ›› ደግሞ እምነት፤አመለካካት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም  በአንድ ላይ ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ/ርቱዕ/ የሆነ እምነት /ሃይማኖት/ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ
  • ‪‎ኦርቶደክስ‬ የሚለው ሥያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙበት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ325ዓ/ም በኒቅያ /በታናሿ እስያ/ የተሰበሰቡት 318ቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡በዚህ ጉባዔ አርዮስ ተወግዟል፡፡
  • ኦርቶዶክስ‬ የሚለው ሥያሜ ከኢትዮጵያና ኦሪየንታል ከሚባሉ አኀት አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ግሪክና ራሽያን የመሳሰሉ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትም ይጠቀሙበታል፡፡ ይህን ሥያሜ ከክርስትና ውጭ የሚገኙ ሌሎች የእምነት ድርጅቶችም የሚገለገሉበት ሲሆን ለአብነት ያህልም እምነታቸውን የሚጠበቁ አይሁዶች እና የሱኒ ሙስሊሞች ኦርቶዶክሶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ስለሆነም ኦርቶዶክስ የሚለው ስያሜ ይልቅ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማንነት ይበልጥ የሚገልጸው ‹‹ ተዋህዶ›› የሚለው ቃል ነው፡፡
  • በኒቂያ‬ እና ኤፎሶን ጉባዔ መካካል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ381ዓ/ም 150 የሚሆኑ ሊቃውንት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የክህደት ትምህርት ይዞ የተነሳውን የመቅዶንዮስን ትምህርት አውግዘዋል፡፡
  • ‹‹ተዋህዶ›› የሚለው ስያሜ መሰረታዊ መነሻው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ431ዓ/ም የተካሄደው የኤፎሶን ጉባዔ ነው፡፡ በዚህም ጉባዔ 200 ሊቃውንት የተገኙ ሲሆን በእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ መናፍቁ ንስጥሮስን ተከራክሮ መልስ በማሳጣት ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ኩራት አጎናጽፏል፡፡
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ የተጠቀሱትን የኒቅያና/325ዓ/ም/፣የቁስጥንጥንያ /381ዓ/ም/ እና ኤፎሶን /431ዓ/ም/ የሃይማኖት ጉባኤያትን እና ውሳኔዎቻቸውን ትቀበላለች፤ስለሆነም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ኦሬንታል ተብለው የሚቃወቁት የግብፅ፣ሶርያ፣ሕንድና የአርመን አብያተ ክርስቲያናት ከኢትዮጵያ/ኤርትራን ጨምሮ/ ቤተ ክርስቲያን ጋር የትምህርት ሃይማኖት እና የታሪክ አንድነት ያላቸውና የተዋህዶ እምነትን የሚከተሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አምስቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባህርይ ነው›› ብለው ስለሚያምኑ የኬልቄዶንን ጉባኤ/451ዓ/ም/ ውሳኔና የሁለት ባህርይ ትምህርት የማይቀበሉና የሚያወግዙ ናቸው፡፡

Friday, March 18, 2016

አምስቱ አዕማደ ምስጢራት/ክፍል አንድ

  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ምን ምን ናቸው?
  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ለምን ምስጢር ተባሉ?
  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት መሠረት ምንድን ነው

                        አምስቱ አዕማደ ምስጢራት
    . ምስጢረ ሥላሴ
    . ምስጢረ ሥጋዌ
    . ምሥጢረ ጥምቀት
    . ምስጢረ ቁርባን
    . ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን

    መግቢያ
    #‹‹አምድ›› ማለት ‹‹ምሶሶ›› ማለት ሲሆን ‹‹አዕማድ››ማለት ደግሞ ምሶሶዎች ማለት ነው፡፡
    #‎አዕማደ ምስጢር ማለት ደግሞ ‹‹የምስጢር ምሶሶዎች ማለት ነው፡፡
    #‎እነዚህ ምስጢራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መሠረታዊ የሆኑ የሃይማኖት አስተምህሮዎች የሚገለጡባቸው ናቸው፡፡
    #እነዚህ ምስጢር ለምን ተባሉ ስንል በጣም ረቂቅና የሰው ልጆች ሕሊና መርምሮ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ከባድ ስለሆኑ ነው፡፡
    #‎እንዲሁም እነዚህ ምስጢራት ለክርስቲኖች ብቻ የሚነገሩ በመሆናቸው ነው፡፡
    #‎የአዕማደ ምስጢር ምንጭና ስያሜ መሰረቱ ምንድን ነው?
    #አዕማደ ምስጢራት ይዘት ምንጭ የጌታና የሐዋርያት ትምህርት ነው፡፡
    #‎ይሁን እንጅ አነሳሱ በጸሎተ ሃይማኖት ወይም አባቶቻችን ምዕመናንን በትክክለኛው ሃይማኖት ለማጽናትና መናፍቃንን ድል ለመንሳት በተካሄዱ በጉባዔ ኒቂያና ቁስጥንጥንያ ነው፡፡
    #‎ከዚህ በኋላ አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጽሃፍት በማውጣጣት አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን አዘጋጅተዋል፡፡
                                                                  ምዕራፍ አንድ
                                                               .ምስጢረ ሥላሴ

    #‹‹ሥላሴ››የሚለው ቃል ‹‹ሠለሰ ሦስት አደረገ ›› ካለው የግዕዝ ግዝ የተገኘ ሲሆን ሦስትነት ማለት ነው፡፡
    #‎ይህ ምስጢር የእግዚአብሔርን አንድነት ሦስትነት የምንማርበት የትምህርት ክፍል ነው፡፡ይህም ልዩ ሦስትነት ይባላል፡፡
    #‎ይህም እግዚአብሔር አንድ አምላክ በሦሰት አካል/ኩነታት ወይም ሁኔታዎች/ ለአበው፣ ለነቢያት ለሐዋርያት የተገለጠውን መሰረት በማደረግ ነው፡፡
    #‎በአጭር ቃል በባህርይ፣በፈቃድና በስልጣን አንድ የሆነውን እግዚአብሔር፣የአካል፣የስምና የግብር ሦስትነት እንዳለው የምናምነው እምነት ምሥጢር ሥላሴ ይባላል፡፡
    .. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት
    #‎የሥላሴ አንድነት፤- በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ይህንን ዓለም ፈጥሮ በማሳለፍ፣በፈቃድ እና በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
    # የሥላሴ ሦስትነት፤- በስም፣በግብርና በአካል ሦስት ናቸው፡፡
                                    ...የሥላሴ ሦስትነት
    #የሥላሴ ሦስትነት በአካል፣በስምና በግብር ነው፡፡
    ....የስም ሦስትነት
    #እነዚህ ሦስት አካላት የየራሳቸው ልዩ ስም አላቸው፡፡
    #‎አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ፡፡አንዳቸው በሌላው ስም አይጠሩም፡፡ይህ ስማቸው ግን ግብራቸውን የሚገልጥ ነው፡፡
    #‹‹ ሂዱና አህዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዝሙራቴ አድርጓቸው››ማቴ፳፰፤፲፱
                                    ....የግብር ሦስትነት
    #‎በግብር አብ ወላዲና አስራጺ፣ወይም መገኛ ነው፡፡ ወልድ ተወላዲ/ከአብ የተገኘ/ መንፈስ ቅዱስም ሠራጺ/ከአብ የወጣ/ ነው፡፡
    #‎ወልድ ከአብ ተወለደ ስንል እምቅድመ ዓለም ነው፡፡
    #ወልድ ስለ ራሱ ሲናገር ‹‹ ምድርም ከመፈጠሯ አስቀድሞ፣ቀላያትም ገና ሳይፈጠሩ፣እኔ ተወለድኩ፣ተራሮች ገና ሳይመሰረቱ፣ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድኩ፡፡››ምሳ፰፤፳፫-፳፭
    #አብ ስለ ባህርይ ልጁ ሲናገር ‹‹ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡›› ማቴ፫፤፲፯
    #‎መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ እኔም አይቸዋለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ፡፡››ዮሐ፩፤፴፬
    #‎ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንትም በሃይማኖተ አበው
    *‹‹ሁሉን የፈጠረ ፣ሰማይና ምድርን ፣የሚጣየውንና የማይታየውን በፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፣እምቅድመ አለም ከአብ በተወለደው ከዓለም በፊት ከአብ ህልው ሆኖ የኖረው፣የአብ አንድ ልጅ በሆነው በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምናለን….ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከባህርይ አምላክ የተገኘ የባህርይ አምላክ ነው የተወለደ እንጅ ያልተፈጠረ››ሃይማኖተ አበው
    *‹‹ አብ ብርሃን ነው፤ከአብ የተወለደ ቃሉ ወልድም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፤ከአብ የሰጠረጸው መንፈስ ቅዱስም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፤ከአብ የወልድ መወለድ .የመንፈስ ቅዱስ መሥረጽ እጅግ ይደንቃል እንጂ አይነገርም ›› ቅዱስ ዲዮናስዮስ
    #‎መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸ ስልን እምቅድመ ዓለም ነው፡፡
    *‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ/ጰራቅሊጦስ/ እርሱም ከአብ የሚወጣ/የሚሰርጽ/ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡››ዮሐ፩፭፤፳፮፤፳፯
    # ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንትም በሃይማኖተ አበው ‹‹ ጌታና ማሕያዊ በሆነው፣ከአብ በሠረፀው በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡ከአብና ከወልድም ጋር በአንድነት እንሰግድለታለን፤እናመሰግነዋለንም››
    #‎ከላይ ቀረበው መንገድ የሦስቱም የየራሳቸው ግብር ወይም ሥራ ይኑራቸው እንጅ ፤ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረው
    #‹‹ አብ አምላክ ነው፣ወልድም አምላክ ነው፤መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፣ነገር ግን ሦስት አማልክት አይባሉም ፤አንድ አምላክ ነው እንጅ›› ቅዱስ አትናቴዎስ
    #‹‹ወልድ ከአብ ተወለደ፣መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ ማለት የፀሃይ ብርሃንና ሙቀት ሁለቱም ከክበቡ ባለመቀዳደም አንድ ጊዜ ተገኙ እንደማለት ያለ እንጅ እንደ ሥጋ ልደት ሕገ ሰብዕን አይከተልም ፡፡
    #‎ስለዚህ በሥጋ ልደት አባት ልጁን እንደሚቀድመውና እንደሚበልጠው አብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም፣ እነርሱም ከአብ አያንሱም፡፡በሥላሴ ዘንድ መቀዳደምም መበላለጥም የለም፡፡
                                                             ....የአካል ሦስትነት
    #‎የአካል ሦስትነት ማለት ሦስቱ አካላት እያንዳንዳቸው ፍጹም አካል፣ፍጹም ገጽ፣ፍጹም መልክ አላቸው ማለት፡፡
    #ይህ አካል ተጨባጭ ወይም ቁሳዊ አካል አካል አይደለም፡፡መንፈሳዊ አካል ነው፡፡ምሳሌ፤-ነፋስ ምንም ዝርው ቢሆንም አካላዊ ነው፣ልንጨብጠውና ልንዳስሰው፣ልናየውም ግን አንችልም ፡፡ባለ መታየቱ ግን የለም ልንለው አንችልም ፡፡ባህር ሲያናውጽ፣ዛፍ ሲወዛውዝ ግን በሥራው መኖሩን እናያለን፡፡
    #‎ከነፋስ የሰው ነፍስ ተረቃለች፣ከሰው ነፍስ የመላዕክት ተረቃለች፣ከመላዕክት ደግሞ የሁሉ ፈጣሪ እግዚብሔር በማይነገር መጠን ረቀቅ ነው፡፡ይህ ረቂቅ አካል የሌለበት ቦታ የለም፡፡
    #የሥላሴ አካል ግን እንደ ነፋስ ዝርው አይደለም፡፡
    #‎ሦስቱ አካላት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በባህርይ፣በህልውና በመለኮት አንድ ናቸው፡፡
    #‎በባህርይ አንድ ናቸው ስንል ሦስቱ አካላት በዘላለማዊነት ፣ሁሉን ቻይነት፣ ምልዕነት፣ረቂቅነትና በመሳሰሉት ነው፡፡
    #በህልውና ማለት በአኗኗር ማለት ነው፡፡
                                                                ...የሥላሴ አንድነት
    #በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ይህንን ዓለም ፈጥሮ በማሳለፍ፣በፈቃድ እና በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
    #በህልውና አንድ ናቸው ስንል አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
    #አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡/ይኖራል/
    #ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ህልው ነው፣
    #መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ውስጥ ህልው ነው፡፡
    *‹‹ፊልጶስ፤ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው፤ኢየሱስም አለው፤አንተ ፊልጶስ ሆይ ይህንን ያህል ዘመን ካንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን?እኔን ያየ አብን አይቷል እንዴትስ አንተ፤አብን አሳይን ትላለህ?እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፡፡እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ››ዮሐ፲፬፤፰-፲፩
    #መለኮት ማለት ገዥነት/መግዛት/ማለት ነው፡፡
    #በመለኮት አንድ ናቸው ስንል በመፍጠር፣ በመስጠት፣በመንሳት፣በማዳን፣በመግደል፣በማጽደቅ፣በመኮነን ይህንን በመሳሰሉ ሁሉ አንድ ናቸው ማለት ነው፡፡
    #ሥላሴ እግዚአብሔር በመባል አንድ ናቸው፡፡
    *‹‹… አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡››ዘዳ ፮፤፬
    #አብ እግዚአብሔር እንደሚባል፤-‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሆን››፪ኛቆሮ፲፫፤፲፬
    #ወልድ እግዚአብሔር እንደሚባል፤- ‹‹ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ-ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ.. ››የሐዋ፳፤፳፰
    #መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚባል፤- ‹‹ጴጥሮስም፤-ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅድስን ታታልል ዘንድ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ ? ›› ቅዱስ ጰጥሮስ ሐናንያን ያታለለው እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን እንደሆነ ነግሮታል፡፡የሐዋ፭፤፫-
    *‹‹አንድ እግዚአብሔር፤አንድ መለኮት ስንል ስለ አብ ስለ ወልድ፣ስለ መንፈስ ቅዱስ መናገራችን ነው፡፡››ዮሐንስ ዘአንጾኪያ

    ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር