Thursday, October 9, 2014

ወርኃ ጽጌ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ወርኃ ጽጌ

ጽጌ የሚለው ቃል ጸገየ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም አበባ ማለት ነው።  በቤተ ክርስቲያን ከመስከረም 26 - ሕዳር 5 ቀን ያሉት አርባ ቀናት “ዘመነ ጽጌ” ይባላል።  በዘመነ ጽጌ ሜዳው፤ ሸንተረሩ በአበባ ያጌጣል።  በክረምቱ ዝናም፤ አረንጓዴ ለብሳ የነበርችው ምድር የተለያዩ ሕብረ ቀለም ባላቸው አበቦች ትሸፈናለች። ጫካው፤ ኮረብታው በአበቦች መዓዛ ይታወዳል። ይህ ወር ጨለማው ክረምት አልፎ ጅረቱ የሚጎድልበት ዘመድ አዝማድ “እንኳን ዘመን ክረምቱን በሰላም አስፈጸማችሁ” እያለ የሚጠያየቅበት ታላቅ የተስፋ መር ነው።


 
  •              በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ) የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ ስንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን) ምንስ እንለብሳለን) ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5÷28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡

  •                 እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.12÷14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡


  •                      በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15 ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11÷1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡
  • ·        የእመቤታችን ስደት እንደ ውሃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም።  ትንቢት የተነገረለት ነው እንጂ፤ ነቢዩ ኢሳ 19፤1 “እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይወርዳል” በማለት ተናግሯል።  በዚህም ግብጽ በስደት ወርዶ ሃገሪቱን መባረኩንና፤ ጣዖታትን መሰባበሩን ሲያጠይቅ ነው።  በዚህ ስደት እመቤታችን ብዙ ችግርና ኃዘን ተፈራርቀውባታል።  የሌሊቱ ቁር የመዓልቱ ሐሩር የአሸዋው ግለት ጽጌረዳ የመሰለ መልኳን አጠውልጎባታል።  ይህንን አባ ጽጌ ማርያም በማህሌተ ጽጌ ድርሰታቸው “ የሮማ ሽቱ የምትሆኚ ማርያም ሆይ በረሃብ፤ አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪጠወልግ ድረስ በልቅሶ እና በስደት የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እህትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህም ፍጻሜ የሌላውን ደስታሽን እካፈል ነበር” ብሏል
  • ·        በወርኃ ጽጌ የሚታሰበው የ እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት ነው።  የጌታን መወለድ በተስፋ ይጠባበቁ የነበሩ”ሰብዓ ሰገል” መወለዱን የሚያበስር ኮከብ “ በምስራቅ አይተው ሊሰግዱለት ወደ ቤተልሔም መጡ። በዚያም የተወለደው የአይሁድ ጌታ የት ነው? እያሉ ጠየቁ።  ይህ ዜና በንጉስ ሄሮድስ ይህንን ያስብ እንጂ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ በቅዱስ ዮሴፍ ወደ ግብጽ እንዲሰደዱ ነገረው።  በዚህም የተነሣ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በምድረ ግብጽ በርሃ ለበርሃ ተንከራተዋል።
  • ·        ይህን ወር የ እመቤታችንን ስደት አስበን በደረሰባት መከራ አዝነን የምናሳልፈው ብቻ አይደለም የራሳችንን ሕይወት የምንቃኝበት የጎበጠውንና የጎደለውን ምግባራችንን ለማቅናት የምንነቃቃበት እንጂ “አምላኬ ተሰዶ ከወጣሁበት ገነት ባይመልሰኝ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነበርኩ” በማለት የምናለቅስበት ጭምር መሆን አለበት።  ሄሮድስ እመቤታችንን ከምድረ ገሊላ ከ እነ ልጇ እንዳሰደዳት ዛሬም በኑፋቄና በትዕቢት በክፋት ተይዘው ከሕይወታቸው እና ከልቦናቸው አውጥተው የሚያሳድዷትም ሁሉ አጥብቀው ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባቸዋል።
  • ·        የጻድቁ ተክለ ሐይማኖት ደቀ መዝሙር የነበሩት አባ ገብረ ማርያም በሰቆቃወ ድንግል ድርሰቱ “ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ዘንዶ ከሔሮድስ ልጅሽ በሸሸ ጊዜ የደረሰብሽን ችግሮች፤ ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትን በአሸዋ ግለት እንዲቆሳስል ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋይም ያለቅስ ነበር።
  • ·        በየቦታው ምድርን ያስጌጠው አበባ እንዳማረበት እንዲሁ አይቀርም ይደርቃል ይረግፋል እኩሌታው ግን ረግፎ አይቀርም ፍሬ ያፈራል። እኛም በተሰጠን ጊዜ በ እምነት አንብበን ፍሬ ምግባርን ልናፈራ ይገባል። ችግርን ሐዘንን የምታውቅ በምልጃም እንዳትለየን እንደ አባ ሕርያቆስ “ ድንግል ሆይ ረሃቡን፤ ጥሙን፤ ችግሩንና፤ ሐዘኑን ከእርሱ ጋር የደረሰብሽን ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ” ልንላት ይገባል።

እመቤታችን ለምን ተሰደደች

ትንቢቱን ለመፈጸም
_       ነቢዩ ኢሳይያስ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ግብጽ በፈጣን ደመና ተጭኖ መውረዱን በትንቢት ሲናገር በነቢዩ ሆሴዕም “ልጇን ከግብጽ ጠራሁት” ብሎ ተናግሯል።  ልጇን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ለጊዜው ለያዕቆብ ሲሆን ፍጻሜው ግን ለአምላከ ያዕቆብ ለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ነበር።

በስሙ ለሚነሱ ቅዱሳን ሰማዕታት ስደትን ባርኮ ለመስጠት
ስደትን ለሰው ልጆች ባርኮ የሰጠው ወልደ አብ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ለመማር፤ለምናኔ፤ ለንስሐ፤ እንዲሁም በሃይማኖት ምክንያት ሃገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ብጹአን ናቸው ማለቱ ነው።

ጣዖት አምልኮን ለማጥፋት
ግብጽ የጣዖት አምልኮ የተስፋፋባት ሃገር ነበረች።  ጣዖት ለማምለካቸውም ብዙ ሕዝብ ተቀስፏል።  ጌታችንም ወደዚያ ቦታ በተሰደደ ጊዜ ጣዖታት ተሰባብረው ጠፍተዋል።

ገዳማተ ግብጽን ለመባረክ
በግብጽ በርካታ የቅድስና ሥፍራዎች አሉ።  እነዚህም ደብረ ቁስቋም፤ ደብረ ምጥማቅ፤ ገዳመ አስቄጥስን፤ ደብረ አባ መቃርስ በመባል የሚታወቁ ሥፍራዎችን ለመባረክ ወደ ግብጽ ተሰደደ።

በተጨማሪ ለማንበብ በዚህ ድረ ገጽ ይጎብኙ

No comments:

Post a Comment

ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር