Sunday, November 23, 2014

ነገረ ማርያም


          ነገረ ማርያም
ነገረ ማርያም፡- ሲል  በእናታችን ቅድስት ድነግል ማርያም በኩል ለሰው ልጅ በእግዚአብሔር  ፈቃድ የተገለጠውን ሁሉ የምንማርበት ትምህርት ነው፡፡በዚህ ትምህትም በሰዎች የመዳን ምስጢር ውስጥ የእመቤታችን የድንግል ማርያም አሰተዋጽኦ የላቀ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የተሰጣት ጸጋ ክብር ስግደት ምስጋና ወዘተ ምን እንደሆነ ዕውቀትእናገኛለን፡፡

ስመ ድንግል ማርያም ትርጓሜ በቤተክርስቲያናችን  

*    ማርያም የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ማሪሃም (ሚርያም) ሲሆን ትርጉሙም እመ ብዙኃን (የብዙዎች እናት) ማለት ነው፡፡በዘፍ.፥፩፯÷፭ አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን (ብዙዎች አባት ) ማለት እንደሆነ፡
*    ማርያም የሚለውን ስም አበው ሊቃውነተ በቤተ ክርስቲያን በምስጢራዊ ዘይቤ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡
ሀ/ ማርያም ማለት መርሕ ለመንግስተ ሰማያት (ወደ መንግስተ ሰመማያት መርታ የምታስገባ)
ምክንያቱም ከሕገ እግዚአብሔር የተራቆተው አዳም ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ ምክንያተ ድኅነት የሆነችው ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ናትና፡፡ወደ መንግስተ ሰማይ መርታየምታስገባ ትባላለች፡፡
ለ/ ማርያም ማለት ጸጋ ወሀብት ማለት ነው
     እመቤታችን ወላጆቿ ለጊዜው በመምከናቸው በሰው ዘንድ ተንቀውና ተዋርደው እነርሱም አዝነው የኖሩ ለነበሩ ታለቅ ሀብት ጸጋ ሆና ተሰጥታለች፤ፍጻሜው ግን አማላጅነቷን አውቀው ቃል ኪዳኗን አምነው ለሚመጡ ምእመናን ሁሉ ሀብት ጸጋ ሆና ተሰጥታዋለች፡፡ ይህም እግዚአብሔር ካንች ጋር ነው በሚለው የመልአኩ ንግግር ታውቋል፡፡ሉቃ.፩፥፳፰-፴
v በበደሉ ምክንያት ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቶ በእግረ አጋንንት ይቀጠቅ የነበረው አዳም ጸጋው ተመልሶለት ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ ያደረገው በእመቤታችን በአእመቤታችን ነውና፡፡
ሐ/ ማርያም ማለት ፍጽምተ ሥጋ ወነፍስ /በድነጋሌ ሥጋ በድነጋሌ ነፍስ የጸናች ፍጽምት/ ማለት ነው፡፡                                           ከነቢብ ከገቢር ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና እናትነትን ከድንግል  ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ ይዛለችና፡፡
       ፍጸምት ማለት ምንም አይነት እንከንና ጉድለትየሌለባት ንጽህተ ንጹሃን ቅድስተ ቅዱሳን አዳማዊ በደል ያልነካት ማኅደረ መለኮት ትሆን ዘንድ የተገባት ማለት ነው፡፡
መ/ ማርያም ማለት መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ/ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ያለች/ ማለት ነው፡፡
    በሥነ ፍጥረት ሕግ መሰረት ከዕለተ እሁድ ጀምሮ እስከ ዕለተ ዓርብ የተፈጠሩ ሁሉ ፍጡራን ይባላሉ፡፡ከነዚህም ፍጡራን መካከልእግዚአብሔር አክብሮና አልቆ የፈጠራቸው ሰውንና መላእክትን ነው፡፡ሰውና መላእክት በተሌክብር መፈጠራቸው ዛሬ ሕጉን አክብረው ስሙን ቀድሰው በኋላ ክብሩን ስለሚወረሱ ነው፡፡
  እመቤታችንን ከፍጡራን የምትልቅ ስንልም ከሰው ልጆችም ሆነ ከመላእክት የምትልቅ የምትከብር ማለታችን ነው፤ምክንያቱም በቅዱሳን መላእክትም ሆነ በቅሳን ሰዎች እግዚአብሔር አድሮባቸው ይኖራል፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ዓለምን ለማዳን ምህረቱን የገለጠባት እመ መሐሪ በመሆኗ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡
  

v ከመላእክት እነደምትበልጥ ‹‹ ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ ….ዓይኖቻቸው ብዙዎች ከሆኑ ከኪሩቤልና ክንፎቻቸው ስድስት ከሆኑ ከሱራፌል ግርማ የሚበለጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፡፡ እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ … ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው አሳት ይድኑ ዘንድ፣ አንች ግን ለመለኮት ማደሪያ ሆነሽየመለኮት ባሕርም አላቃጠለሽም፡፡ የእሳት ነበልባልን ተሸከምሽ፡፡›› በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ምስክርነት ያስረዳል፡፡
v ከሰው ልጆችም እነደምትበልጥ‹‹ከቅዱሳን ክብር የእመቤታችን ክብር ይበልጣል አካላዊ ቃልን ለመቀበል በቅታ ተገኝታለችና መላእክት የሚፈሩትን ትጉኃን በሰማያት የሚያመሰገኑትን ድንግል ማርያም በማህጸኗ ቻለችው፡፡››በማለት ቅዱስ ኤፍሬም መስክሯል፡፡
/ ማርያም ማለት እግዝእተ ብዙኃን /የብዙዎች እመቤት/ ማለት ነው፡፡ 
·        ከአዳምና ሔዋን ውድቀት በኋላ የሰው ዘር በሙሉ በዲያቢሎስ የኃጠአት አገዛዝ ስር ወድቆ ነበር የዚያ ዘመነ ፍዳ መገለጫም አዳም የዲያቢሎስ ወንድ ባሪያ ሔዋን የዲያቢሎስ ሴት ባሪያ ናት የሚለው የመከራ ማኅተም ነበር፡፡የዚያ ጊዜ ፍጻሜው ሲደርስ ከመለእኩ እመቤታችን የሰማችው ድምጽ‹‹ከሴቶች ተለይረሽ የተባረክሽ ነሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይደስ የበልሽአግዚአብሔር ከአነች ጋር ነውና፡፡››በማለቱ በሔዋን ምክንያት የገባ ስህተትና መርገም ሁሉ በልጇ ይሻር ዘንድ እግዚአብሔር ከሥጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ነገረን፡፡
እመቤት ማለት በአንድ ቤተሰብ መካከል አስተዳዳሪና ኃላፊ ማለት የሆነች ታላቅ ሴት ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም በክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ያመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ በክርስቶስ አነድ ቤተሰብ በመሆናቸው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እመቤታቸው ናት፡፡
ረ/   ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ማለት ነው፡፡
           አካለዊ ቃል በእመቤታችን ማኅጸን አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መለኮትን ከትስብእት (ከሥጋ) ትስብእትን ከመለኮት አዋሕዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ስለተገለጠባት ለአምላክ ሰው የመሆኑ ምክንያት ፣ ለሰው የመዳኑ ምክንያት ናትና ተላኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ትባላለች፡፡የሰውን ወደ እግዚአብሔር፣ የእግዚአብሔርንም ይቅርታ ወደ ሰው በማድረስ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ፣በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለደችታሰጣለችና፡፡
            

No comments:

Post a Comment

ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር