Friday, March 18, 2016

ወላጆችና የልጆች አስተዳደግ/ክፍል አንድ/

ልጆች ''ብዙ ተባዙ'' በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ከእግዚአብሔር የሚገኙ በረከቶች ናቸው።
ቅዱስ ዳዊት “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናችው”(መዝ ፻፳፮፥፫) እንዳለ። ቅዱሳን ፣ ጻድቃን፣ ጳጳሳት ፣ ካህናት፣ ነገሥታት እና መሣፍንት የሚገኙት ከዚሁ አምላካዊ በረከት ነው።
የወላጅነት ምንነት
ወላጅነትን ስንተረጉም “ቤተሰብ” የሚለውን ቃል አጽንኦት ልንሰጠው ይገባል። “ቤተሰብ” የሚለውን ቃል ለመግለጽ የተለያዩ ፍቺዎች ተሠጥተዋል። እነዚህም፡-
  • “ቤተሰብ ከእናትና ከአባት እንዲሁም ከልጆች የተዋቀረ ቡድን ነው።”
  • “ቤተሰብ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ልጆችን የሚያሳድግና የሚያስተምር ተቋም ነው።
  •  የማኅበረ ሰብም ሥረ መሠረት ተደርጎም ይቆጠራል።”
የወላጅነት ትርጉም
ወላጅነት ማለት የቤተ ሰብ ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ማለት ነው።
ወላጅነት ልጆችን የማሳደግ ጥበብ/ክኅሎት የሚጠይቅ ሥራ ማለትም ጭምር ነው። ወላጅነት ልጆች ከሚፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ውስብስብ የሆነና አወንታዊ ተጽእኖ ለማምጣት ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ ተግባር ነው።
የወላጅነት ምንነት
በቅዱስ መጽሐፍ ብዙ እናቶች እና አባቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ በማሳደግ በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ክብር አግኝተዋል።አባታችን አብርሃም ለልጆቹ እና በእርሱ ሥር ለሚተዳደሩት ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ እየፈጸመ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩ በማዘዝ ሙሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ያደረግ ነበር።በመሆኑም ይስሐቅ ለአባቱ አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ለሚያቀርበው መባዕ መሥዋዕት እስከመሆን ድረስ ታዘዘ (ዘፍ፳፪፥፩-፲፪)። ሙሴ ከእናቱ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እና የወገንን ፍቅር ሰለተማረ እግዚአብሔርም ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት በሙሴ መሪነት አወጣ።በአንጻሩ ግን ሊቀ ካህናት ኤሊ የራሱ ሕይወት የማይነቀፍ ቢሆንም ልጆቹ አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ፊት የማይገባቸውን በማድረጋቸው እና እርሱም እነርሱን አጥብቆ በመገሠጽ ከክፉ መንገድ እንዲመለሱ ባለማድረጉ ምክንያት በበረከት ፋንታ ሁሉም መርገም ደርሰባቸው(፩ኛሳሙ ፬፥፩)።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ልጆች ሆይ፥
1. ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” (ኤፌ ፮፥፩-፬) እንዳለ።
                                                      የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎች
1. ወላጅ መር የአስተዳደግ ዘይቤ
ይህ አይነቱ የአስተዳደግ ዘይቤ ተፅዕኖኣዊ ሲሆን የሚከተሉት ገፅታዎች ይታዩበታል ፡፡
የወላጅ /አሳዳጊ/አምባገንነት፣
ጥያቄ የማይቀረብበት ፣ ማብራሪያ የማይጠየቅበት እና ሀይለ ቃልና ትዕዛዝ የበዛበት ገጽታ ያለው ነው፡፡
1.1. ወላጅ መር የአስተዳደግ ዘይቤ;
 በሕፃናት ላይ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች /ውጤቶች/ ህፃናቱ በፍርሀትና በጭንቀት እንዲዋጡ ያድርጋል፣ ህጻናቱ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ያደርሳል፣ የህፃናቱ የመጠየቅና የማወቅ ፍላጎት ይገታል፣ ተገዢነትን ያረጋግጣል፣ ህፃናቱ የራሳቸውን ሀሳብና ውሳኔ መስጠት እንዲሳናቸው ያደርጋል፣በራስ መተማመንን በህፃናቱ ዘንድ ይቀንሳል፣ ህፃናቱ ሁልጊዜም ከራስ ተነሳሽነት ይልቅ ትዕዛዝ ጠባቂዎች እንዲሆኑ ያደርጋል፣
እንዲሁም በህፃናቱ የወደ ፊት ህይወት ማህበራዊ ሕይወትና ግንኙነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም ይህን የአስተዳዳደግ ዘይቤ ተግባራዊ ማድረግ በህፃናቱ ላይ ዘለቄታ ያለው አውንታዊ የባህሪ ለውጥ ማምጣትና መግራት እጅግ አዳጋች ነው፡፡
2. መረን የለሽ /ልቅ/ የሆነ የአስተዳደግ ዘይቤ
ይህ የአስተዳደግ ዘይቤ ከላይ ከተጠቀሰው የወላጅ መር የአስተዳደግ ዘይቤ ተፃራሪ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህ የአስተዳደግ ዘይቤ የሚጠቀሙ ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊዎች ህፃናቱን አቅጣጫ የማስያዝና የመቆጣጠር ሃላፊነትን አያሳዩም ህፃናቱን ስለአኗኗራቸውና ውሎአቸው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲሰጡ ኃላፊነትን እንዲወስዱ ያደርጋሉ፡፡ ለህጻናቱ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነትን ይሰጣሉ፡፡
ይህ የአስተዳደግ ዘቤ በሕፃናቱ ተፈጥሮአዊ ስሜትና ችሎታ እንዲሁም ተሳትፎ ላይ እምነት መጣሉ እንደጥሩ ጎን ቢታይም ብቻውን ማለትም አለአዋቂዎች ክትትል፣ተሳትፎና እገዛ የሚፈለገውን የባህሪ ለውጥ /ስነ-ምግባር/ ለማምጣት አያስችልም፡፡
2.2. መረን የለሽ አስተዳደግ ዘይቤ በህፃናቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ
  • ህፃናት ደንብና ሥርዓት ለመከተልና አካባቢያቸውን በሚገባ ለማወቅ ፣ብሎም ራሳቸውን የመቆጣጠር ልማድ ለማዳበር የአዋቂዎች እገዛ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ህፃናት በየደረጃው ሊያከናውኑ የሚገባቸውን መደበኛ ፣አካላዊ ማህበራዊ ሚናን በራሳቸው አቅጣጫ ለመገንዘብና ያዩትንም ሆነ የሰሙትን ለመተግበር ስለሚንቀሳቀሱ ተገቢ ወደ አልሆነ ድርጊት ወይም መንገድ በቀላሉ በመግባት ለአደጋ ስለሚጋለጡ፣
3. አሳታፊያዊ የአስተዳደግ ዘይቤ
ይህን የአስተዳደግ ዘይቤ የሚጠቀሙ ወይም የሚተገብሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥያቄ መልካም ምላሽ ፣ድጋፍ፣ፍቅር በውይይትና በምክር ተገቢውን ፈር እና አቅጣጫ የሚያስይዙ ናቸው፡፡ ይህ ስልት አዋቂዎች ለህፃናት ደንቦችንና መጠበቅ ያለባቸውን ስርአቶች እስከ ምክንያቶቻቸው በግልፅ የማስረዳትና የማስገንዘብ ሁኔታን ያመላክታል፡፡ በዚህ ዘዴ የልጅና የወላጅ አለበለዚያም ያሳዳጊ ተሰሚነትና ተቀባይነት ስር የሰደደ ነው፡፡
3.1. አሳታፊያዊ የአስተዳደግ ዘይቤ የሚከተሉትን ባህሪያት ይይዛል፡፡
  • የህፃናትን ፍላጎት ያካትታል ፣ መከበር የሚገባቸውን ደንቦች ፣መብቶችና ግዴታዎች ይገልፃል:: ከግዴታዎች በስተጀርባ ያሉትን ምክንያቶች የሚያብራራና ለውይይት ክፍት የሆነ ዘይቤ ነው፣ ህፃናት ባህላቸውን አውቀው እንዲያዳብሩ ይረዳል፣ ህፃናት እንዲጠይቁ ፣መረጃ እንዲያገኙ እና አስተያያት እንዲሰጡ ያደርጋል፣ ከኃይለ ቃልና ከዱላ ይልቅ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ነው፣
በወላጅ /በአሳዳጊዎች / እና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ ነው፣ በህፃናት ላይ የማወቅንና በራስ የመተማመን ስሜት ያዳብራል፣ እንዲሁም በቤት ውስጥና በቤተሰብ መካካል ሰላምንና መረጋጋትን ያሰፍናል ፡፡
4. ቁብ የለሽ የአስዳደግ ዘይቤ

ይህ የአስተዳደግ ዘይቤ የሚከተሉት ባሀሪያት አሉት፡፡ ለህፃናት ፍቅርና ቅርበትና አያሳይም እንክብካቤም አያደርግም በአብዛኛው ግድየለሽ ፣አግላይና አጣጣይ ወላጆች የሚጠቀሙበትን የአስተዳደግ ዘይቤ ነው ፡፡ የደንታ ቢስ ዘይቤ ነው ተብሎ መደምደም ይቻላል፡፡የህፃናቱን ዞር ብሎ ካለማየት ፣ ከማግለል እስከ በደል ማድረስ ይደርሳል፡፡ ይህን የአስተዳደግ ዘይቤ የሚከተሉትን ወላጆች በአብዛኛው ቅድሚያ የሚሰጡት የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ ለልጆቻቸውጊዜ የላቸውም ልጆቻቸውንም ዞር ብሎ የማየትም ልምድ አይኖራቸውም፡፡

No comments:

Post a Comment

ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር