Friday, March 18, 2016

አምስቱ አዕማደ ምስጢራት/ክፍል አንድ

  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ምን ምን ናቸው?
  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ለምን ምስጢር ተባሉ?
  • አምስቱ አዕማደ ምስጢራት መሠረት ምንድን ነው

                        አምስቱ አዕማደ ምስጢራት
    . ምስጢረ ሥላሴ
    . ምስጢረ ሥጋዌ
    . ምሥጢረ ጥምቀት
    . ምስጢረ ቁርባን
    . ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን

    መግቢያ
    #‹‹አምድ›› ማለት ‹‹ምሶሶ›› ማለት ሲሆን ‹‹አዕማድ››ማለት ደግሞ ምሶሶዎች ማለት ነው፡፡
    #‎አዕማደ ምስጢር ማለት ደግሞ ‹‹የምስጢር ምሶሶዎች ማለት ነው፡፡
    #‎እነዚህ ምስጢራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መሠረታዊ የሆኑ የሃይማኖት አስተምህሮዎች የሚገለጡባቸው ናቸው፡፡
    #እነዚህ ምስጢር ለምን ተባሉ ስንል በጣም ረቂቅና የሰው ልጆች ሕሊና መርምሮ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ከባድ ስለሆኑ ነው፡፡
    #‎እንዲሁም እነዚህ ምስጢራት ለክርስቲኖች ብቻ የሚነገሩ በመሆናቸው ነው፡፡
    #‎የአዕማደ ምስጢር ምንጭና ስያሜ መሰረቱ ምንድን ነው?
    #አዕማደ ምስጢራት ይዘት ምንጭ የጌታና የሐዋርያት ትምህርት ነው፡፡
    #‎ይሁን እንጅ አነሳሱ በጸሎተ ሃይማኖት ወይም አባቶቻችን ምዕመናንን በትክክለኛው ሃይማኖት ለማጽናትና መናፍቃንን ድል ለመንሳት በተካሄዱ በጉባዔ ኒቂያና ቁስጥንጥንያ ነው፡፡
    #‎ከዚህ በኋላ አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጽሃፍት በማውጣጣት አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን አዘጋጅተዋል፡፡
                                                                  ምዕራፍ አንድ
                                                               .ምስጢረ ሥላሴ

    #‹‹ሥላሴ››የሚለው ቃል ‹‹ሠለሰ ሦስት አደረገ ›› ካለው የግዕዝ ግዝ የተገኘ ሲሆን ሦስትነት ማለት ነው፡፡
    #‎ይህ ምስጢር የእግዚአብሔርን አንድነት ሦስትነት የምንማርበት የትምህርት ክፍል ነው፡፡ይህም ልዩ ሦስትነት ይባላል፡፡
    #‎ይህም እግዚአብሔር አንድ አምላክ በሦሰት አካል/ኩነታት ወይም ሁኔታዎች/ ለአበው፣ ለነቢያት ለሐዋርያት የተገለጠውን መሰረት በማደረግ ነው፡፡
    #‎በአጭር ቃል በባህርይ፣በፈቃድና በስልጣን አንድ የሆነውን እግዚአብሔር፣የአካል፣የስምና የግብር ሦስትነት እንዳለው የምናምነው እምነት ምሥጢር ሥላሴ ይባላል፡፡
    .. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት
    #‎የሥላሴ አንድነት፤- በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ይህንን ዓለም ፈጥሮ በማሳለፍ፣በፈቃድ እና በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
    # የሥላሴ ሦስትነት፤- በስም፣በግብርና በአካል ሦስት ናቸው፡፡
                                    ...የሥላሴ ሦስትነት
    #የሥላሴ ሦስትነት በአካል፣በስምና በግብር ነው፡፡
    ....የስም ሦስትነት
    #እነዚህ ሦስት አካላት የየራሳቸው ልዩ ስም አላቸው፡፡
    #‎አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ፡፡አንዳቸው በሌላው ስም አይጠሩም፡፡ይህ ስማቸው ግን ግብራቸውን የሚገልጥ ነው፡፡
    #‹‹ ሂዱና አህዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዝሙራቴ አድርጓቸው››ማቴ፳፰፤፲፱
                                    ....የግብር ሦስትነት
    #‎በግብር አብ ወላዲና አስራጺ፣ወይም መገኛ ነው፡፡ ወልድ ተወላዲ/ከአብ የተገኘ/ መንፈስ ቅዱስም ሠራጺ/ከአብ የወጣ/ ነው፡፡
    #‎ወልድ ከአብ ተወለደ ስንል እምቅድመ ዓለም ነው፡፡
    #ወልድ ስለ ራሱ ሲናገር ‹‹ ምድርም ከመፈጠሯ አስቀድሞ፣ቀላያትም ገና ሳይፈጠሩ፣እኔ ተወለድኩ፣ተራሮች ገና ሳይመሰረቱ፣ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድኩ፡፡››ምሳ፰፤፳፫-፳፭
    #አብ ስለ ባህርይ ልጁ ሲናገር ‹‹ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡›› ማቴ፫፤፲፯
    #‎መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ እኔም አይቸዋለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ፡፡››ዮሐ፩፤፴፬
    #‎ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንትም በሃይማኖተ አበው
    *‹‹ሁሉን የፈጠረ ፣ሰማይና ምድርን ፣የሚጣየውንና የማይታየውን በፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፣እምቅድመ አለም ከአብ በተወለደው ከዓለም በፊት ከአብ ህልው ሆኖ የኖረው፣የአብ አንድ ልጅ በሆነው በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምናለን….ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከባህርይ አምላክ የተገኘ የባህርይ አምላክ ነው የተወለደ እንጅ ያልተፈጠረ››ሃይማኖተ አበው
    *‹‹ አብ ብርሃን ነው፤ከአብ የተወለደ ቃሉ ወልድም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፤ከአብ የሰጠረጸው መንፈስ ቅዱስም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፤ከአብ የወልድ መወለድ .የመንፈስ ቅዱስ መሥረጽ እጅግ ይደንቃል እንጂ አይነገርም ›› ቅዱስ ዲዮናስዮስ
    #‎መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸ ስልን እምቅድመ ዓለም ነው፡፡
    *‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ/ጰራቅሊጦስ/ እርሱም ከአብ የሚወጣ/የሚሰርጽ/ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡››ዮሐ፩፭፤፳፮፤፳፯
    # ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንትም በሃይማኖተ አበው ‹‹ ጌታና ማሕያዊ በሆነው፣ከአብ በሠረፀው በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡ከአብና ከወልድም ጋር በአንድነት እንሰግድለታለን፤እናመሰግነዋለንም››
    #‎ከላይ ቀረበው መንገድ የሦስቱም የየራሳቸው ግብር ወይም ሥራ ይኑራቸው እንጅ ፤ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረው
    #‹‹ አብ አምላክ ነው፣ወልድም አምላክ ነው፤መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፣ነገር ግን ሦስት አማልክት አይባሉም ፤አንድ አምላክ ነው እንጅ›› ቅዱስ አትናቴዎስ
    #‹‹ወልድ ከአብ ተወለደ፣መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ ማለት የፀሃይ ብርሃንና ሙቀት ሁለቱም ከክበቡ ባለመቀዳደም አንድ ጊዜ ተገኙ እንደማለት ያለ እንጅ እንደ ሥጋ ልደት ሕገ ሰብዕን አይከተልም ፡፡
    #‎ስለዚህ በሥጋ ልደት አባት ልጁን እንደሚቀድመውና እንደሚበልጠው አብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም፣ እነርሱም ከአብ አያንሱም፡፡በሥላሴ ዘንድ መቀዳደምም መበላለጥም የለም፡፡
                                                             ....የአካል ሦስትነት
    #‎የአካል ሦስትነት ማለት ሦስቱ አካላት እያንዳንዳቸው ፍጹም አካል፣ፍጹም ገጽ፣ፍጹም መልክ አላቸው ማለት፡፡
    #ይህ አካል ተጨባጭ ወይም ቁሳዊ አካል አካል አይደለም፡፡መንፈሳዊ አካል ነው፡፡ምሳሌ፤-ነፋስ ምንም ዝርው ቢሆንም አካላዊ ነው፣ልንጨብጠውና ልንዳስሰው፣ልናየውም ግን አንችልም ፡፡ባለ መታየቱ ግን የለም ልንለው አንችልም ፡፡ባህር ሲያናውጽ፣ዛፍ ሲወዛውዝ ግን በሥራው መኖሩን እናያለን፡፡
    #‎ከነፋስ የሰው ነፍስ ተረቃለች፣ከሰው ነፍስ የመላዕክት ተረቃለች፣ከመላዕክት ደግሞ የሁሉ ፈጣሪ እግዚብሔር በማይነገር መጠን ረቀቅ ነው፡፡ይህ ረቂቅ አካል የሌለበት ቦታ የለም፡፡
    #የሥላሴ አካል ግን እንደ ነፋስ ዝርው አይደለም፡፡
    #‎ሦስቱ አካላት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በባህርይ፣በህልውና በመለኮት አንድ ናቸው፡፡
    #‎በባህርይ አንድ ናቸው ስንል ሦስቱ አካላት በዘላለማዊነት ፣ሁሉን ቻይነት፣ ምልዕነት፣ረቂቅነትና በመሳሰሉት ነው፡፡
    #በህልውና ማለት በአኗኗር ማለት ነው፡፡
                                                                ...የሥላሴ አንድነት
    #በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ይህንን ዓለም ፈጥሮ በማሳለፍ፣በፈቃድ እና በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
    #በህልውና አንድ ናቸው ስንል አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
    #አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡/ይኖራል/
    #ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ህልው ነው፣
    #መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ውስጥ ህልው ነው፡፡
    *‹‹ፊልጶስ፤ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው፤ኢየሱስም አለው፤አንተ ፊልጶስ ሆይ ይህንን ያህል ዘመን ካንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን?እኔን ያየ አብን አይቷል እንዴትስ አንተ፤አብን አሳይን ትላለህ?እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፡፡እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ››ዮሐ፲፬፤፰-፲፩
    #መለኮት ማለት ገዥነት/መግዛት/ማለት ነው፡፡
    #በመለኮት አንድ ናቸው ስንል በመፍጠር፣ በመስጠት፣በመንሳት፣በማዳን፣በመግደል፣በማጽደቅ፣በመኮነን ይህንን በመሳሰሉ ሁሉ አንድ ናቸው ማለት ነው፡፡
    #ሥላሴ እግዚአብሔር በመባል አንድ ናቸው፡፡
    *‹‹… አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡››ዘዳ ፮፤፬
    #አብ እግዚአብሔር እንደሚባል፤-‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሆን››፪ኛቆሮ፲፫፤፲፬
    #ወልድ እግዚአብሔር እንደሚባል፤- ‹‹ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ-ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ.. ››የሐዋ፳፤፳፰
    #መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚባል፤- ‹‹ጴጥሮስም፤-ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅድስን ታታልል ዘንድ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ ? ›› ቅዱስ ጰጥሮስ ሐናንያን ያታለለው እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን እንደሆነ ነግሮታል፡፡የሐዋ፭፤፫-
    *‹‹አንድ እግዚአብሔር፤አንድ መለኮት ስንል ስለ አብ ስለ ወልድ፣ስለ መንፈስ ቅዱስ መናገራችን ነው፡፡››ዮሐንስ ዘአንጾኪያ

    No comments:

    Post a Comment

    ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር