Friday, June 20, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት


በዲያቆን ንጋቱ አበበ
ሃይማኖት የሚለው ቀጥተኛ ትርጉሙ እምነት ማለት ሲሆን ይኸውም የነገረ መለኮትን ትምህርት፤ የአምልኮትን ሥርዓት ከእምነትም የተነሣ የሰውን አካሄድ ያጠቃልላል 2 ጢሞ 47:: በተጨማሪም ሃይማኖት ማለት እግዚአብሔርን አውቀን በእውነትና በትክክል መንገድ ተመርተን የምናመልክበት ነው። 

 ምክንያቱም በሃይማኖት ያለው መንገድ ፈጽሞ የማይለወጥና ፍጹም የሆነ የማያረጅ፤ የማይቀየር እና እንከን የሌለበት ዘለዓለማዊ እውነት መንገድ ነው:: ይህንንም ሃይማኖት ያስተማረን እርሱ የሚታዩትንና የማይታዩትን ፍጥረታትን በሙሉ ካለመኖር ወደ መኖር የፈጠረ ከመላእክት፤ ከሊቃነ መላእክት፤ ከአጋእዝትና ከሥልጣናት ከኪሩቤልም ከሱራፌልም በላይ የሚኖር፤ እርሱም ከፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ከምስጋና ሁሉ በላይ ልዑል የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ነው:: አምላካችን ያስተማረን እውነተኛይቱ ሃይማኖት አንዲት ብቻ እርሷም ተዋሕዶ ናት ኤፌ 4:5:: ተዋሕዶ ስንል አምላክ የሰው የሆነበት ሰውም አምላክ የሆነበት ምስጢር የተከናወነበት የተፈጸመበት ነው:: ዮሐ 1 1-14:: እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ያስተምረናልና ሲነግረንም ሲያስተምረንም የማይለወጠውን የማይሻረውን የሃይማኖት ፍሬ በሕይወታችን ይዘን እንድንሄድ የሚያስተምሩን፤ ከሃይማኖት ፈቀቅ እንዳንል የሚመክሩን አባቶችን በየዘመኑ እያስነሣ በሥነ ፍጥረት፤ በነቢያት፤ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ፤ በመንፈስ ቅዱስና በቅዱሳት መጽሐፍት አስተምሮናል:: በሃይማኖት ከኖርን መላ ሰውነታችን ለእርሱ እናስገዛለንእንቀደሳለንኑሮአችን በሙሉ ይባረካል:: " እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር እራሳችሁን ጠብቁ" ይሁ 1:20:: ይህ የሚያስረዳን የሚያስተምረን የሚያረጋግጥልን በተቀደሰ እውነት ውስጥ የመኖር ጥበብ የሚገኘው በሃይማኖት መሆኑን ብቻ ነው:: ለዚህም ነው ካህኑ በቅዳሴ ማርያም ላይ አቤቱ ሁሉን ለፈጠርክለማትታይ አምላክ ለአንተ ሰውነታችንን እንዘረጋለንሁሉን ለምታዋርድ ለአንተ ራሳችንን እናዋርዳለን፤ ሁሉን ለምታሰግድ ለአንተ እንሰግዳለን፤ ሁሉን ለምትገዛ ለአንተ እንገዛለን ሲሉ ዲያቆኑ ደግሞ በፍርሃት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ስገዱ ይላል፤ ሕዝቡም ተቀብሎ አቤቱ በፊትህ እንሰግዳለን እናመሰግንሃለንም ብለው ይሰግዳሉ:: በተቀደሰ እውነትና ሕይወት ውስጥ በሃይማኖት መኖር ማለት በእንደዚህ አይነት መልኩ ሲኖር ብቻ ነው::

አምስቱ አዕማደ ምሥጢር
ምሥጢር ማለት የተደበቀ፤ የተሸሸገ ነገር፤ ለማንም የማይገለጥ የተሰወረ ብሂል ማለት ነው።
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድን ስንመለከት፤ ልዑል እግዚአብሔርአምላካችን ሰማይንና ምድርን ካለመኖር ወደ መኖር ብቁ የሆነ ሥነ-ፍጥረት የፈጠረበትን ሁኔታ በዚሁ ምዕራፍ እንገነዘባለን። እግዚአብሔር አምላካችን ቅድመ ዓለም ከሁሉም በፊት የነበረ፤ፍጥረታትን የፈጠረና ፈጥሮ የሚገዛ፤ ያለ፤ የሚኖር፤ ይህን ዓለም አሳልፎም የሚኖር፤ ለእርሱ ግን አስገኝ አሳላፊ የሌለው መሆኑን፤በአንድነት በሦስትነት ያለ፤ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ የሚያሳውቀንና የሚያስረዳን  ነው፡፡
ስለዚህ አምስቱ አዕማደ ምሥጢርን በሃይማኖት፤ በእምነት ካልተቀበልነው በስተቀር የሰው አዕምሮ መርምሮ ከቶ የማይደርስበት የፈጣሪ የአምላክ ሥራ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷን የምትገልጽበት፤ የምታስተምርበትና የምትመሰክርበት አምስት አዕማደ ምሥጢር አላት።  እነዚህም
1) ምሥጢረ ሥላሴ
2) ምሥጢረ ሥጋዌ
3) ምሥጢረ ጥምቀት
4) ምሥጢረ ቁርባን
5) ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
ማንኛውም ክርስቲያን እነዚህን አምስቱ አዕማደ ምስጢራትን ጠንቅቆ መረዳት ይገባዋል ምክንያቱም የእምነታችን መሰረት ስለሆነ።
1) ምሥጢረ ሥላሴ
ዘፍ 1 26 ላይ እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር።
http://www.mkyzg.org/resources/silase.jpg
ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ፤ ሥላሴ በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ማለታቸውእንዴት ነው ቢሉ:: 

ሥላሴ ለባውያን፣ነባብያን፣ሕያዋን ናቸው ስለዚህም አዳም ለባዊ፣ነባቢ፣ሕያው ነው ማለት ነው። ይህም ማለት የሰው ነፍስ በልብነቷ የአብ ምሳሌ ናት፤ በቃልነቷ የወልድ ምሳሌ ናት፤ በሕያውነቷ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት።  የነፍስ ልብነቷ ቃልነቷን እና ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለች፤ ቃልና ሕይወት ከአንዲት ከልብ ስለተገኙ ግን በከዊን ልዩ እንደሆኑ በመነገርም ይለያሉ። አብ ወላዲ (ወለደ) ይባላል፤ ቃል ተወላዲ (ተወለደ) ይባላል፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ይባላል። ይህም ማለት አብ ወልድን በቃል አምሳል ወለደ፤ መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስ አምሳል አሰረጸው።  ነፍስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች እንጂ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷና እስትንፋስነቷ በኋላ አልተገኙም።  አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አይበልጥም፤ ወልድም አብንና መንፈስ ቅዱስን አይበልጥም፤ መንፈስ ቅዱስም አብንና ወልድን አይበልጥም። አብ ወልድን ሲወልደው፤ መንፈስ ቅዱስን ሲያሰርጸው አይቀድማቸውም። ሰው በነፍስ በዚህ አኳኋን የሚመስለው ስለሆነ እግዚአብሔርሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠርአለ።
ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፤ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው። 
ሥላሴ፤ በሥም፤ በአካል፤ በግብር፤ ሦስት ናቸው።
የስም ሦስትነታቸውም፤ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ነው ማቴ 2819
እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው
የአካል ሦስትነታቸው፤  አብ የራሱ የሆነ አካል አለው፤ ወልድ የራሱ የሆነ አካል አለው፤ መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካል አለው። ማቴ 3 16-17
ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ታየ፤ እነሆም ድምጽ ከሰማይ መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።  ይህ ደግሞ ሥላሴ በአካል ሦስት መሆናቸው በዮርዳኖስ በጥምቀት ጊዜ አረጋግጦልናል። ወልድም እራሱ ተጠማቂ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ በተለየ አካሉ በርግብ አምሳል ሲወርድ፤ አብ በደመና አምሳል መጥቶ ለወልድ የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ በማለቱ በአካል ሦስት መሆናቸውን ገልጸውልናል።
   የግብር ሦስትነታቸውም፤ አብ አባት፤ ወልድ ልጅ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ነው
አብ ወልድን ወለደ ማለት ከአካሉ ከባሕርይው ተገኘ ማለት ነው። ለምሳሌ የሰው ነፍስ ልብነቷ ቃልነቷን እንደሚያስገኝ ነው።  ወልድ ከአብ ተወለደ ማለት አብን አህሎ መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው።  ለምሳሌ የነፍስ ቃልነቷ ከልብነቷ እንደተገኘ ነው። አብ መንፈስ ቅዱስን አሰረጸው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው ተገኘ ማለት ነው። ለምሳሌ የነፍስ ልብነቷ ሕይወቷን እንዳስገኘው ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸ ሲባል አብን አህሎ መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው። ዮሐ 1516 “ እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እሱ እኔ ይመሰክራል።
በመለኮት፤ በአገዛዝ፤ በሥልጣን፤ ይህን ዓለም በመፍጠርና በማሳለፍ ደግሞ አንድ ናቸው።  ለዚህም ማስረጃ
ማጠቃለያ (ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በጥቂቱ)
ምሥጢረ ሥላሴ የእግዚአብሔር አንድነት እና ሦስትነት የሚገለጽበት ነው።  እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፤ ሦስት ሲሆን አንድ ነው ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ያስረዳናል።
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ዘፍ 126
እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ።  ዘፍ 322 ከእኛ የሚለውና እንደ አንዱ የሚለውን ቃላቶች ወይም አባባሎችን ስንመለከት እግዚአብሔር ከአንድ በላይ እንደሆነ የሚጠቁሙን አባባሎች ናቸው።
ኑ፥ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። ዘፍ 116 እንውረድ የሚለውን ቃላት ስንመለከት አሁንም ከአንድ በላይ መሆኑን ነው።
ዘፍ 181-15 ላይ አብርሃም በሥላሴ እንዴት እንደተባረከ፤ እግዚአብሔርን በአንድነት እና በሦስትነት እየገለጸ ከፈጣሪው ጋር በግልጽ እየጠራው እንመለከታለን። ይኸውም እግዚአብሔር በመምሬ አድባር ሥር ለአብርሃም ተገለጠለት።  አብርሃምም ሦስት ሰዎችን ተመለከተ፤ ሊቀበላቸውና ወደ ቤቱ ጠርቶ ለማስተናገድ ፈጥኖ ሄደ፤ እንደደረሰም ሰገደላቸው፤ ቀጠለና በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ ብሎ አንድነቱን መሰከረ ከዚያም በመቀጠል ውሃ ይምጣላችሁ በማለት በአካል ሦስት መሆናቸውን ገለጸ።  በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በእግዚአብሔር እና በአብርሃም መካከል ያደረጉትን ቃለ ምልልስ  ስንመለከት ወይም ስናነብ አብርሃም እግዚአብሔርን በአንድነቱና በሦስትነቱ ሲጠራ እንመለከታለን።  በይበልጥ ይህ ታሪክ የሚያስረዳን እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፤ ሦስት ሲሆን አንድ ነው የምንለውን ከአምሥቱ አዕማደ ምሥጢር የመጀመሪያውን ምሥጢረ ሥላሴን  ግልጽ አድርጎ ያስረዳናል።
በዮሐንስ ራዕይ 48 እና በኢሳይያስ 61-3 ላይ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ይላል ይህ ማለት ደግሞ ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ቃላት ነው ምክንያቱም አንዱ ቅዱስ ለአብ፤ ሁለተኛው ቅዱስ ለወልድ፤ ሦስተኛው ቅዱስ ደግሞ ለመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ብቻ ነው።
  2 ቆሮ 1314 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ላይ እንዲህ ይላል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
የእግዚአብሔር አንድነት እና ሦስትነት እንዴት ነው ቢሉ?
ማስረጃ፤
የእግዚአብሔር አንድነት
በሥልጣን፤  የዮሐንስ ወንጌል 1030 ላይ እኔና አብ አንድ ነን አለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በሕልውና፤ የዮሐንስ ወንጌል 1410 ላይ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ አለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በመለኮት፤
በአገዛዝ፤
ይህን ዓለም በመፍጠርና በማሳለፍ፤  ዘፍ 11 ላይ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ እንጂ ፈጠሩ አይልም
በልብ (አብ) በቃል (ወልድ) በእስትንፋስ (መንፈስ ቅዱስ) መዝ 321-6 ላይ  የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች፤ እግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ ሰራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ ይላል።
በባሕርይ
በፈቃድ
          እግዚአብሔር ሦስትነት
የስም ሦስትነት፦ በስም፤ በአካል በግብር ማቴ 2819 ሂዱና አህዛብን በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።
የግብር ሦስትነት፦ አብ አባት፤ ወልድ ልጅ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ፤ አብ ወልድን ወለደ። ወልድ ከአብ ተወለደ ማለት አብን አህሎ መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው። አብ መንፈስ ቅዱስን አሰረጸው ማለት ከአካሉ ከባህሪው ተገኘ ማለት ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረፀ ሲባል አብን አህሎ መስሎ ተገኘ ማለት ነው። ዮሐ 1526
የአካል ሦስትነት፦ አብ የራሱ የሆን ፍጹም መልክ፤ ፍጹም ገጽ አለው፤ ወልድ የራሱ የሆነ ፍጹም መልክ፤ ፍጹም ገጽ አለው፤ መንፈስ ቅዱስም የራሱ የሆነ ፍጹም መልክ፤ ፍጹም ገጽ አለው።  ማቴ 316-17

ከብዙ በጥቂቱ ይህን ያክል ከገለጽኩ ተጨማሪ እውቀትን ለመጨበጥ ደግሞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትን ጠይቃችሁ እውቀታችሁን በመያዝ በእምነት ጸንታችሁ ዘለዓለም በቤቱ እንድንኖር እርሱ ፈጣሪ ይርዳን። 

ሥላሴ በስም በአካል በግብር ሦስት ናቸው ብንልም በአገዛዝ፤ በሥልጣን፤ በባህሪይ፤ በፈቃድ፤ በመለኮት፤ ይህን ዓለም በመፍጠርና በማሳለፍ፤ በሕልውና አንድ ስለሆኑ አንድ አምላክ ተብሎ ይታመናል፤ ይጠራል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም ከዚህም የተነሳ ሥላሴ ሦስት ሲሆኑ አንድ፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት በመሆናቸው ይህ ምሥጢር ተባለ ለሚያምን ብቻ የሚገለጽ ምሥጢር ነው።

 የምስጢር ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ምሥጢሩን ይግለጽልን አሜን።




No comments:

Post a Comment

ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር