Thursday, January 29, 2015

በዓለ እረፍታ ለእግዝእትነ ማርያም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!!
  በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእረፍት በዓል መታሰቢያ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጻፈው አምላክን የወለደች እናታችንና እመቤታችን የምትሆን ቅድሰት ድንግል ማርያምን ለዚሁ ለተወደደ ተማሪው የአደራ የጸጋ እናትነት እርሱን ደግሞ ለእርሷ ከሀዘኗ ያረጋጋት ያጽናናት እንዲሁም ያገለግላት ዘንድ በአደራ ልጅነት ሰጥቷታል፡፡ የሐ19፤27 ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ከፋፍለው ለማስተማር እስከሄዱበት ድረስ ከዚያ በኋላም በኢየሩሳሌም ከቀሩት መምህራን ሐዋርያትና ቅዱሳንት አንስት ጋር በጸሎትታቸውም በጉባዔቸውም መካከል እየተገኘች ለአስራ አራት ዓመታት ከእነርሱ ጋር ቆይታለች፡፡ሐዋርያው ማትያስ በይሁዳ ምትክ ለሐዋርያነት ሲመረጥና መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ከእነርሱ ጋር በጸሎት እንደነበረች ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ በሐዋርያት ስራ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ዮሐ1፤14 እመቤታችን በዚህ በልጇ ሞት/በታላቅ ሀዘኗ ወቅት/ እና ከዚያም በኋላ በጌታችን መቃብር በጐልጐታ በጸሎት እየሄደች ህማሙን፣ሞቱን እያስታወሰች ታነባና ታለቅስ ነበር፡፡በዚህ ቦታ ስታለቅስ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እየተገለጸ ያረጋጋትና ያጽናናት እንደነበረም በግብረ ህማማት መጽሃፍ ተጽፏል፡፡( ግብረ ህማማት ዘእሁድ ገጽ442-444) እንደተለመደው በመቃብሩ ስትጸልይ ከዚህ ዓለም እንደምትለይ መንፈስ ቅዱስ ነገራት፤ገለጸላት፡፡ለሐዋርያና ለቅዱሳት አንስትም በያሉበት‹‹ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የተሸከመችኝን፣ሦስት ዓመት እያጠባች ያሳደገችኝን እናቴ ማርያምን ወደ እኔ እወስዳታለሁ፡፡››ብሎ ዜና እረፍቷን አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡እነርሱም ‹‹አንተ ካረግህ ጀምሮ በሀዘን በኖርን ነበር፡፡ነገር ግን እናትህ በመካከላችን እያረጋጋችንና የእግዚአብሐርን ቃል እየነገረችን በፍጹም ደስታ አንተን እያመሰገን ኑረን ነበር፡፡አሁንስ ለምን ከእኛ ትለያታለህ?እኛንስ ለምን እናትና አባት እንደሌላቸው ታደርገናለህ?››ሲሉ ለምነውታል፡፡ጌታችንም ‹‹ከእናቱ ማህጸን የወጣ ሁሉ ይሞታል፡፡እኔም ሙቸ ነበር፤ሞትን ግን ድል አድርጌ ተነሳሁ፤እንዱሁም እናቴ ማርያምም እንደ ሰው ሁሉ ትሞታለች ከዚያ በኋላ በታላቅ ክብር ከሙታን ትነሳለች፡፡››ብሎ መለኮታዊ ውሳኔውን አስረድቷቸዋል፡፡/መጽሐፈ ግንዘት ገጽ10-11/
ጥር 20 ቀን ጌታ ሐዋርትን ከያሉበት ሰበሰባቸው፡፡እመቤታችንም ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹ሂዱና ስጋየ ይገነዝበት ዘንድ የበፍታ ልብስ አምጡልኝ በደብረ ዘይት ወደ ሚኖሩ ደናግላንም ላኩና ይምጡ ከእኔም ጋር ይደሩ፡፡››አለቻቸው፡፡ሁለት በፍታ ልብሶችን አመጡላት ደናግላን መጥተው መብራታቸውን አብረተው መዝሙረ ዳዊትናንና  ማህሌተ ነበያትን ዙርያዋን ከበው ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ ሲያደርሱ አድረዋል፡፡እመቤታችን የመግነዝ ልብሶችን መሬት ላይ ዘርግታ ‹‹ጌታየና አምላኬ የእስራኤልና የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ የሰራህ አንተ ነህ፡፡ ዛሬ የምለምንህን ስማ የአገልጋይህን ነፍስ ወደ ህይወት ምራት›› እለች እየጸለየች ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋ መላእክት አጅበውት እያመሰገኑት መጥቶ አረጋጋት ያዘጋጀላትን ተድላዋንና ደስታዋን ነገራት፡፡
ከዚህ ዓለም የምትለይበት ሰዓት በደረሰች ጊዜ ሐዋርያትና ደናግላን ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት፡፡እጇን በላያቸው ዘርግታ ባርካቸዋለች፡፡ከልጇ ቃል ኪዳን ከተቀበለች በኋላ ጥር21 ቀን በ47ዓ/ም በ64 ዓመቷ በእለተ እሁድ ዐርፋለች፡፡በእናት በአባቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሦስተ ወር፣በቤተ መቅደስ አስራ ሁለት ዓመት በወንጌላዊው ዮሐንስ ቤት አስራ አራት ዓመት ኑራለች፡፡
ንጽሕት ነብሷን በልብሰ ብርሃን አጎናጽፎ ያሳረገ እርሱ እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡በዚች ዕለትም ታላላቅ ተዓምራት ተደርገዋል፡፡
የእመቤታችን አማላጅነቷ፣እናትነቷ፣ፍቅሯ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!!


No comments:

Post a Comment

ደ/ም/አ/ቤ/ቅ/ገ/ሰ/ት/ቤት ጎንደር