
1. ጾመ ኢየሱስ፡-መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በመጣ ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ በዲያቢሎስም ተፈትኖ የጾምን ኃይል አሳይቶበታል ፡፡ፈታኙም በስስት ቢመጣበት በትዕግስት በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ፡በፍቅረ ንዋይ ቢፈትነው በጸሊአ ንዋይ ድል ነስቶታል ፡፡እኛም የፈጣሪያችን በረከት ያድርብን ዘንድ ለጾሙ ልዩ ቦታ ሰጥተን እንጾመዋለን፡፡
2. ጾመ ድህነት፡-ከበዓለ 50 ውጭ በሳምንት ረቡዕ እና አርብ የሚጾመው ነው ፡፡ረቡዕ የአይሁድ ቤተ-መንግስትና ቤተ-ክህነት ክርስቶስን ይገድሉት ዘንምክራቸውን ያጸኑበት ዕለት ሲሆን አርብ ደግሞ ለቤዛ ዓለም በስጋ የተገለጠው አምላክ የከበረ ስጋውን ቆርሶ ቅዱስ የሆነዉን ደሙን አፈስሶ መላውን ዓለም ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ዕለተ አርብን በጾም እናከበረዋለን፡፡
3. ጾመ- ገሃድ ፡-በዓመት አንድ ጊዜ በጥምቀት ዋዜማ የሚጾም ሲሆን ከስሙም ትርጓሜ ስንነሳ ገሀድ ያልነ እንደሆነ የተገለጠ፤የታየ የሚለውን ትረጉም ይሰጠናል፡፡ይኸም በጥምቀቱ የአንድነቱን የሦስትነቱን ምስጢር በገለጠልን ዋዜማ የሚጾም ጾም በመሆኑ ነው፡፡
4. ጾመ- ሐዋርያት ፡-ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰማያዊ ተልዕኮ ስለተሰጣቸው ከ50 ቀናት በኋላ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማግስት መጾም ጀመሩ፡፡የአበው ቀደምትን አሰረ ፍኖትን የምትከተል ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ትንሳኤ በዋለ በ50ኛው ቀን የጾሙን አዋጅ እንዲሁ ለልጆቿ አውጃለች፡፡
5. ጾመ ነቢያት፡- ከልደት በዓል በፊት ባሉት 44ዕለታት የሚጾመው ነው፡፡ይኸም ጾም የነቢያት ትንቢት መፈጸሙን የ5500 የመከራ ዘመን ማብቃቱን እያሰብን የምንጾመው ጾም ነው ፡፡
6. ጾመ ነነዌ፡-በየዓመቱ ከጾመ ሁዳዴ 15 ቀን ቀድሞ ከሰኞ እስከ ረቡዕ የሚጾም ጾም ሲሆን፡፡ ጾሙም የነቢዩ ዮናስን ስብከት የሰሙ የነነዌ ሕዝቦች ንስሃ ገብተው በእሳት ከመቀጣት የዳኑበት ነዉ፡፡ እኛም በሰውነታችን ክፋት ምክንያት አታጥፋን በማለት ሦስቷን የነነዌ ጾም በጾምና በጸሎት ሆነን እናሳልፋለን፡፡
7. ጾም ፍልሰታ፡-በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ለሁለት ሱባዔ የሚቆይ ጾም ነው፡፡ጾሙ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የእመቤታችን አስከሬን እንዲሰጣቸውና በክብር እንዲቀብሩት እንዲሁም ትንሳኤዋን ለማየት የጾሙት ጾም ሲሆን እኛም የእመቤታችን በረከት ይደርብን ስንል የኸንን ጾም በፍቅር እንጾመዋለን፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ጊዜ አብይ ጾምን በስፋት እናቀረባዋለን፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና ትውፊት እና ሥርዓት መሠረት በዘንድሮው ዓመት ሰኞ የካቲት 9/2007 የሚጀመረው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡
በቀጣይ ስለ አቢይ ጾም ሳምንታት በዝርዝር እናቀርባለን፡፡
No comments:
Post a Comment